የሻው ስንሻው

መስከረም 02/2016 ዓ.ም

ኢትዮጵያ ከቀደምት እና ጥንታውያን ባለ ታሪክ አገራት አንዷ ስለመሆኗ አንስቶ መጣል የዚህ ጽሑፍ ዓላማ አይደለም፡፡ የሥርዓተ መንግሥት እና የአገረ መንግሥት ግንባታ ታሪካችንም የዚያኑ ያህል በዋዛ ጀምሮ ለማጠናቀቅ አይሞከርም፡፡ አሁን እስከምንገኝበት ዘመን ድረስ በኢትዮጵያ ላይ ስለተፈራረቁት አገዛዞች ለመተረክም ይዤ የተነሳሁት አጀንዳ ይፈቅድልኝ አይመስለኝም፡፡ የታሪክ ጉዟችን ግን ምርትና ግርድ እንደማያጣው አምናለሁ፡፡ ሰዎች ወደ ፖለቲካ ሥልጣን የሚማትሩት ለጽድቅ ሥራ ለመትጋት በማሰብ አይደለም፡፡ ቤተ መንግሥት እና መንግሥተ ሠማያት እየቅል እንደመሆናቸው የፖለቲካው ሜዳ ሸፍጥና መጠላለፍ አያጣውም፡፡ ይህንን እውነታ ገዥዎቻችንም  ሆኑ እኛ ተገዥዎቻቸው ጠንቅቀን እንረዳዋለን፡፡

የታደሉት አገራት ዜጎች መሪዎቻቸውን በድምጽ መስጫ ካርዳቸው ተጠቅመው ለቤተ መንግሥት ሲያበቁ፤ በአመጽ፤ በጦርነት እና እንዲያም ሲል በመፈንቅለ መንግሥት ገዥዎች በሕዝብ ጫንቃ ላይ ፊጥ የሚሉባቸው አጋጣሚዎች ካልታደልነው ከእኛ እና ብጤዎቻችን መንደር ይዘወተራል፡፡ የይስሙላ ምርጫ ማካሄድ፤ ምርጫ ማጭበርበር፤ ሕዝቡን አማራጭ በመንፈግ የሥልጣን ቆይታ ገድብን እና ዕድሜን በመለጠጥ እንዲያም ሲል  ሕገ መንግሥትን በመከለስ ከቤተ-መንግሥት ምቾት ሞት ወይም ስደት የሚገላግላቸውም ገዥዎች ሞልተዋል፡፡ ሥዩመ እግዚአብሔር ለመሰኘት በመቃጣት ሕዝቡ ላይ እንደ መዥገር በመጣበቅ ደሙን የሚመጥጡ ገዥዎች ጉዳይም ቢሆን በተለይም አዳጊ አገራት ፈውስ ያላገኙለት ውርዴ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ አራት ሚሊየን ተኩል  የአገር ውስጥ ተፈናቃይ እንዲሁም 21 ሚሊየን የዕለት ደራሽ ዕርዳታ ጠባቂ ዜጎች በሚገኙባት አገር ለግዙፍ እና ቅንጡ አብያተ-መንግሥት ግንባታ የሚተጉ ገዥዎች ሥልጣንን ለልጅ ልጆቻቸው ጭምር በውርስ የማስተላለፍ ዕቅድ እንደሌላቸው ሊያስረዱን የሚችሉት በማፈናቀል፤ በማፈን፤ በማሰር እና በመግደል የተካኑት የዙፋን ጠባቂዎቻቸው ብቻ ናቸው፡፡ ጦርነት እየዘሩ፤ እልቂት እያዘመሩ ሰቆቃን የሚቀልቡን ገዥዎች የከፋቸው ቀን መደበቂያቸውን ከአገር ውጭ እያደራጁ መሄጃ የሌለውን ምስኪን ሕዝብ በሐሰት ትርክት አንዱን ከሌላው ጋር በፈረቃ እያጋጩ እና እያፋጁ ዕለት ዕለት እጆቻቸውን በንጹሐን ደም ያጨቀያሉ፡፡ 

የገዥዎቻችንን አንድም የማን አለብኝነት አለበለዚያም የመሰሪነት ወይም የሁለቱ ድቅል የሆነ አጀንዳ ሕዝቡ በጊዜ ተገንዝቦ አብሮ እና ተባብሮ “ከእንግዲህ ይበቃል” ካላለ በስተቀር የእልቂቱ ጽዋ በወር ተራ የእያንዳንዱን ደጅ ማንኳኳቱ አይቀሬ መሆኑ በውል እየታየ ይገኛል፡፡ የሕወሓት ጀብደኝነት መነሻ ሆነና ትግራይ፤ አፋር እና አማራ የጦርነት ቋያ ተቀጣጠለባቸው፡፡ ይህ ጦርነት የመሠረተ ልማት ውድመትን፤ የኤኮኖሚና ማኅበራዊ መዋቅሮች መፍረስን ብቻ አልነበረም ያስከተለው፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎቻችንን አካልና ነፍስ ገብረንበታል፡፡ ይህንን ጦርነት በአሸናፊነት መወጣት የኢትዮጵያውያንን የዴሞክራሲ፤ የፍትሕ እና እኩልነት ጥያቄ በአግባቡ የሚመልስ እንደሚሆን እስከ እርግጠኝነት የዘለቀ እምነት አሳድረው የነበሩ ዜጎች ቁጥር ቀላል አልነበረም፡፡ እንዲህ ባለ ፍጥነት ሌላ አውዳሚ ጦርነት በአማራ ሕዝብ ላይ ይታወጃል የሚል ግምት ከገዥዎቹ በስተቀር ማንም ሊኖረው ባይችል አያስገርምም፡፡ የዛሬዎቹ ዓይን አውጣ የፖለቲካ ቁማርተኞች እየቆመሩብን የሚገኘው በሚሊየኖች ኢትዮጵያውያን ሕይወት እና የነገ ተስፋ ላይ ጭምር መሀኑን ልብ ይሏል፡፡ ራሳቸውን ከሕግ እና ሥርዓት በላይ አድርገው የሚቆጥሩት እኒህ ቁማርተኞች አገራችንን በወለድ አግድ እንዳላስያዟት ምንም ማረጋገጫ የለንም፡፡ ለኃይል ማመንጫ ግድቦቻችን ወጭ ከተደረገው የበለጠ በጀት የተመደበላቸው የአብያተ መንግሥት ግንባታ ሥራዎች ኦዲት እንዳይደረጉ፤ የበጀት ምንጫቸው ግልጽ እንደማይደረግ እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ቢሆን ጉዳዩ እንደማይመለከተው በድፍረት ይናገራሉ፡፡ ይህን ጉዳይ የነሱት የፓርላማው የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እስከነ አለመከሰስ መብታቸው ዘብጥያ ወርደዋል፡፡ ሁኔታዎች በዚህ ከቀጠሉ አገር ሊያሳጡን እንደሚችሉ በመስጋት የችግሩ ገፈት ቀማሽ ለሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለመሰንዘር ተገድጃለሁ፡፡

የኦሮሞ ሕዝብ ሆይ፡– በማንኛውም ጊዜ ገዥዎች የሕዝብን ስም ለሥልጣን መወጣጫ እንደ መሰላል ይጠቀሙታል እንጂ የሹመቱን እርካብ ከተቆናጠጡ በኋላ መለስ ብለው አያስታውሱትም፡፡  ኦሮምኛ ተናጋሪ ገዥ ቤተ-መንግሥት ስለገባ እና ዙፋን ላይ ስለተሰየመ ብቻ ኦሮሞ ወርቅ ይዘንብለታል ማለት አይደለም፡፡ ጥቂቶች ዘርፈው ኃብት ስላግበሰበሱ የኦሮሞ አርሶ አደር ወይም አርብቶ አደር ወይም ላብ አደር ኑሮው ተደላደለለት የሚያስብል አንዳችም አመክንዮ የለም፡፡ እዚህ ላይ በኦሮሞ ስም የሚምሉት እና የሚገዘቱት ሹማምንት ወደ ሥልጣን ከመጡ ጀምሮ በተለያዩ የኦሮሞ አካባቢዎች እየተፈጸሙ የዘለቁትን ግፎች በእማኝነት ጨረፍ በማድረግ መሟገት ይቻላል፡፡ 

የቦረና ሕዝብ ለአራት ዓመታት  በተከታታይ በድርቅ የተመታው እና የቤት እንስሳቱ እንዳሉ የረገፉበት በኦሮሞ ልጆች የአገዛዝ ዘመን አይደለምን? ለገጽታ ግንባታ ይበልጡን በማሰብ ስለ ድርቁ ትንፍሽ እንዳይባል እና ረኃብ ለጠናበት ሕዝብ እርዳታ በወቅቱ እንዳይደርስለት የተደረገው የቦረና አርብቶ አደር ምን በደል ቢኖርበት ነው? ላለፉት አምስት ዓመታት የወለጋ ሕዝብ እስከነ መፈጠሩ የተረሳ ይመስላል፡፡ ልጆቹ ከትምህርት ገበታ ተለይተዋል፡፡ የጤና አገልግሎት አያገኝም፡፡ የግብርና ሥራውን በወጉ ማከናወን አልቻለም፡፡ ይህም አልበቃ ብሎ ቀን ቀን ለመንግሥት ታጣቂ፤ ሌቱን ደግሞ ለአማጽያን ይገብራል፡፡ በሁለቱም ወገን ስለማይታመን ይታሰራል፤ ይገረፋል፤ ይሰደዳል፤ ይገደላል፡፡፡ በሰሜን ሸዋ፤ በምዕራብ ሸዋ፤ በደቡብ ምዕራብ ሸዋ፤ በምሥራቅ ሸዋ፤ በምዕራብ አርሲ፤ በጉጂ፤ በቡኖ በደሌ፤ በኢሉ አባቦራ እና በሌሎችም አካባቢዎች  የሚሆነው ከወለጋ እምብዛም የተለየ አይደለም፡፡ እንግዲያው፤ኑሯቸውን ላትኖር እና ኑሮህንም ላይኖሩ በስምህ የሚነግዱ ሥልጣን አሳዳጆች፤ ዘራፊዎች እና ገራፊዎች ፍትሕን፤ ርትዕን፤ ወንድማማችነትን እና እኩልነትን ያሰፍኑልኛል ማለት ዘበት ይሆናል፡፡ ይልቁኑ አንተን ከተቀሩት ኢትዮጵያውያን ወገኖችህ ደም አቃብተውህ ሲያበቃ ሹማምንቱ በዘረፉት ኃብት የተደላደለ ኑሮ ለመምራት ከአገር ወጥተው ሊኮበልሉም ይችላሉ፡፡  ስለዚህ፤ በከፋፋይ ፕሮፓጋንዳቸው ሳትታለል ለእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘህ የበኩልህን ድርሻ ለመወጣት ራስህን የምታዘጋጅበት ጊዜ አሁን ካልሆነ መቼ ሊሆን ይችላል?

የአዲስ አበባ ሕዝብ ሆይ፡- በሰው ሠራሽ መንገድ የሕዝብ አሰፋፈር ሥርዓቱ እንዲዛባ በስፋት እና በክፋት እየተሠራ ይገኛል፡፡ የፌደራል ፖሊስ እና መከለላከያ የደኅንነት መሥሪያ ቤቱንም ጨምሮ፤ የከተማ አስተዳደሩ እና የኦሮሚያ አንጋቾች በተናጠልም ይሁን በጣምራ ከየአቅጣጫው ሰቅዘው ይዘውሃል፡፡ በዚያ ላይ ሪፐብሊካን ዘብ ሲታከልበት በከተማዋ ሠማይ ስር የሰፈነው የስጋት ደመና ያስጨንቃል፡፡ ማን፤ ለምን፤ የት አፍኖ እንደሚወስድህ አታውቀውም፡፡ ስለምን ሲባል ጥፍርህን በጉጠት እየነቀለ ሰቆቃ እንደሚፈጽምብህ አይገባህም፡፡ ሽንቱን እላይህ ላይ እየሸና ሰው መሆንህን እንድትጠላ የሚያደርግህ ለምን እንደሆነ አይነግርህም፡፡ የትኛው ወንጀልህ ለኢሰብዓዊ አያያዝ እንደዳረገህ አታውቀውም፡፡ ወደ ግል እስር ቤቶች እና በማጎሪያ ካምፖች እየተወረወረክ ለምን  በኮሌራ እና ተስቦ እንድትሞት እንደሚፈረድብህ አታውቀውም፡፡ አንድ በውል የሚታወቅ ጉዳይ ግን አለ፡፡ እርሱም ይህ ድርጊት የሰልቃጭ አምባገነኖች የወል መገለጫ መሆኑ ነው፡፡

የከተማዋ ወሰን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተኮማተረ በመሄድ ላይ መሆኑ ሳያንስ የጥሪት ቅሚያ እና ሽሚያ አሳሳቢ ከሚባለው ደረጃ በላይ ገዝፏል፡፡ ጣውንት ከተማ የመፍጠሩ ሥራ ቀጥሏል፡፡ በውኃ አቅርቦት እቀባ ለማስፈራራትም ዳር ዳር ማለት ተጀምሯል፡፡ በኑሮ ውድነት እና በቀለብ እጥረት የመቅጣት ስልት የሙከራ ትግበራ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ በጥቅሉ የከተማ አስተዳደሩ በእነ ማን እንደሚዘወር ገሃድ ወጥቷል፡፡ ሁኔታዎች በዚህ ከቀጠሉ ለጥቆ ስለሚሆነው ነገር ለመተንበይ ነብይ መሆንን አይጠይቅም፡፡ አዲሳቤ ሆይ፤ ጊዜው ሁለት ምርጫ ሰጥቶሃል፤ መሆን ወይም አለመሆን! የሚሻልህን የምታውቀው ግን አንተ ነህ፡፡

የትግራይ ሕዝብ ሆይ፡- እንመራሃለን በሚሉ ሰዎች የነጠፈ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም እና የመከነ አስተሳሰብ ከአንዱ ጦርነት ወደ ሌላው እየተሸጋገርህ እፎይታ አጥተህ መዝለቅህ የተቀረው ኢትዮጵያዊ ወገንህ ሁሉ መራር ትውስታ እንደ ሆነ እናውቃለን፡፡ የውድ ልጆችህ መስዋዕትነት አስተማማኝ ሠላም እና ዘላቂ ዕድገት ሊያጎናጽፍህ አልቻለም፡፡ ተጋድሎህ የትግራይን እናቶች እንባ ከማበስ ይልቅ ማለቂያ በሌለው የእልቂት አዙሪት ውስጥ ከመግባት አልታደገህም፡፡ ሞተህ ያኖርካቸው እና ተዋግተህ ለሥልጣን ያበቃኻቸው ልጆችህም ቢሆኑ የራሳቸው ምቾት እንጂ የአንተ ጉስቁልና ግድ እንደማይሰጣቸው አንተው ራስህ ሕያው ምስክር ነህ፡፡ ከትግራይ አዋሳኝ ወገኖችህ ጋር ደም እንድትቃባ ተደርገሃል፡፡ አሁን ደግሞ ሴማዊነትንህን እንደ ወንጀል የሚቆጥር የኩሽ ጦር እየተሰበቀብህ ይገኛል፡፡ እንግዲያውስ የዴሞክራሲ፤ የፍትሕ እና እኩልነት ጥያቄ ካነገቡ ሌሎች ኢትዮጵያውያን ወገኖችህ ጋር በመሰለፍ አገርህን አድን፤ የሰቆቃውን አዙሪትም ሰብረህ ውጣ፡፡ ለጋራ ችግሮቻችን የጋራ መፍትሔ በአብሮነት ማፈላለግ ካልቻልን መጭው ጊዜ ከቀደመውም የከፋ ሊሆን እንደሚችል ልብ እንበል፡፡

የሶማሌ ሕዝብ ሆይ፡- አገዛዙ ወንድምህ ከሆነው ከአፋር ሕዝብ ጋር ደም እንድትቃባ ሤራ ይጎነጉንልሃል፡፡ ድሬ ዳዋን በተመለከተ ቋሚ ውዝግብ ደቅኖብሃል፡፡ ከሐረርጌ አንስቶ በባሌ አድርጎ ቦረናን ይዞ እስከ ሞያሌ ባለው ሰፊ መልክአ ምድር ወገንህ ከሆነው የኦሮሞ ሕዝብ ጋር በወሰን ጉዳይ እንድትቃቃር በአገዛዙ አማካይነት ተንኮል ታስቦበት እና ታቅዶ ይተገበርብሃል፡፡ ይህ ቋሚ ስጋት መቼ ወደ ለየለት ወረራ እንደሚሸጋገር ማንም ማረጋገጫ አይኖረውም፡፡ ከተቀረው ኢትዮጵያዊ ወገንህ ጋር በመናበብ ለፍትሕ፤ እኩልነት እና ዴሞክራሲ ለሚደረገው ትግል የድርሻህን ካልተወጣህ ሊመጣ ያለው አደጋ በተናጠል የሚመከት አይመስልም፡፡ 

የሲዳማ ሕዝብ ሆይ፡- በመልጌ ወንዶ፤ በወንዶ ገነት፤ በብላቴ በኩል፤ በጭሪ፤ በግርጃ እና በሌሎችም አካባቢዎች ሰልቃጩ አገዛዝ የደቀነብህ የወሰን ላይ መፈናቀል እና መገዳደል ማብቂያ ሳይበጅለት ዘልቋል፡፡ አሁን ደግሞ በአዋሣ ከተማ ላይ የይገባኛል ጥያቄ እየተነሳ ይገኛል፡፡ ይህን አደገኛ የጠቅላይነት ግስጋሴ መግታት እስካልቻልን ድረስ ራሳችንን ለባርነት አሳልፈን እንደ ሰጠን አይቆጠርምን?

የአፋር ሕዝብ ሆይ፡- አገዛዙ በስልት እና ስሌት ከትግራይ፤ ከሶማሌ፤ ከኦሮሞ አዋሳኝ ወንድሞችህ ጋር በፍቅር እና ትብብር ለጋራ ጥቅም እንዳትመካከር ወደ ግጭት እያንደረደረህ እና የተረጋጋ ሠላም እንዳይኖርህ ሲሠራ ሰንብቷል፡፡ በአፋር ሕዝብ ላይ የሚደረገው ወከባ አንድምታ ሕዝቡ ለኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት ያለው ጽናት እና ቀናዒነት እንደ ሆነ ጥርጥር የለውም፡፡ እንደዚህ ዓይነቱ ግጭት ጠማቂነት የገዥዎችን የሥልጣን ዕድሜ እና የሰፊውን ሕዝብ የመከራ ዘመን ከማርዘም በቀር የአገርን ልማት እና የሕዝብን አንድነት አያረጋግጥም፡፡ ስለዚህ፤ አብረን እና ተባብረን የጋራ አገራችንን ከተያያዘችው የቁልቁለት መንገድ መመለስ የለብንምን?

የጋምቤላ ሕዝብ ሆይ፡- የጋምቤላ ምድር እንደ በሽታ ጊዜ ጠብቆ የሚያገረሽ የደም ግብር አለበት፡፡ ግጭቶቹን የሚዘውሩት ስውር እጆች ከአገዛዙ የሚሰነዘሩ ስለመሆናቸው ጥርጥር የለውም፡፡ በቀደመው ጊዜ ጋምቤላ ከክልሎች የአንዱ አካል ሆኖ ካርታ ተሠርቶለት እንደ ነበር ይታወሳል፡፡ ባለፈው ሰሞን ደግሞ በክልሉ ውስጥ የእሬቻ በዓል እንዲከበር ትዕዛዝ ተላልፎ ተተግብሯል፡፡ ነገ ተነገወዲያ ደግሞ ጋምቤላ የኢሉ አባቦር ወይም የወለጋ አንዱ ክፍል ተደርጎ የማይጠቀለልበት ምክንያት አይኖር ይሆናል፡፡ ይህን ጠቅላይ አካሄድ በአንድነት ቆመን “ይበቃል” ካላልነው በስተቀር መጨረሻው የት ያደርሰን ይመስላችኋል?

የቤንሻንጉል ጉሙዝ ሕዝብ ሆይ፡- በብሐራዊ ደረጃ እየተቀነቀነ የሚገኘው የቁጥር ጨዋታ አሁን ቤንሻንጉል ጉሙዝ ደርሷል፡፡ “ከክልሉ ነዋሪ ሲሶው እኛ ነን” ተብላችኋል፡፡ በማኦ ኮሞ፤ በአሶሣ እና  በካማሼ አካባቢ የሚታየው ወሰን ማስፋት መዳረሻው የት ሊሆን እንደሚችል በውል ማጤን የተገባ አይመስላችሁምን? በዚህ ባሕርይው ይህ አሁን በአገራችን የሰፈነው አገዛዝ ለሁላችንም እኩል የሆነች ኢትዮጵያ እውን ያደርግልናል ብለን ራሳችንን ከማሞኘት እንቅልፍ አሁኑኑ ካልነቃን እጅጉን ይረፍድብን ይመስለኛል፡፡ 

የጉራጌ ሕዝብ ሆይ፡- የመደመጥ አቅምህን ለማዳከም ሲባል ስልጤ እንዲለይህ ተደረገ፡፡ አሁን ደግሞ ከመስቃን፤ ከማረቆ፤ ከወለኔ እና ከቀቤና እየተጋጨህ አንድነትህን እንድታጣ እየተሠራ ይገኛል፡፡ ተገቢ ጥያቄዎችህም ሰሚ ጆሮ የተነፈጋቸው በጉራጌ ሕዝብ ላይ ይህ እንዲሆን ስለሚፈለግ ነው፡፡ ውኃ ተጠምተው ባዶ ጀሪካን ይዘው ለሰልፍ አደባባይ የወጡትም ሆኑ የመሠረት ድንጋይ ከተጣለ በኋላ ደብዛው ስለጠፋው የሆስፒታል ፕሮጀክት ለመጠየቅ ትዕይንተ ሕዝብ ያደረጉ የጉራጌ ልጆች በጭካኔ ተገድለዋል፡፡ ይባስ ብሎ አገዛዙ በሶዶ በኩል ወረዳውን ሊጠቀልል ስለፈለገ ብቻ ለተደጋጋሚ የሽብር ጥቃት እና ጭፍጨፋ እንድትዳረግ ፈርዶብሃል፡፡ የዚህ ሁሉ ግፍ እና መከራ ማቆሚያ እና ማክተሚያው የት ላይ ይሆን?

የሐረሪ ሕዝብ ሆይ፡- ክልሉን በተመለከተ ውሳኔ የመስጠት መብትህ እስከ ምን ድረስ እንደሆነ አንተው ታውቀዋለህ፡፡ መሪዎችህ እየተሳደዱ እና እየተሸማቀቁ እንዲኖሩ እየተደረገ ስለመሆኑ ልነግርህ አልፈልግም፡፡ የገዥዎችን ሕገ-ወጥ ጫና አሜን ብለህ እስካልተቀበልክ ድረስ በውኃ ጥም እንድታልቅ ተፈርዶብህ እንደ ነበር የቅርብ ትዝታህ ነው፡፡ አሁን ደግሞ ከአያት ቅድመ አያትህ የእርሻ ማሣ እየነቀሉ ያባርሩህ ይዘዋል፡፡ ለመሆኑ ከዚህ ቀጥሎ ሊመጣብህ የሚችለው መከራ ምን ሊሆን እንደሚችል አስበኸው ታውቃለህ? መፍትሔውስ?

የጌዴኦ ሕዝብ ሆይ፡- በ2010 ዓ.ም የለውጡ ማግስት በሚሊዮን የሚቆጠር የጌዴኦ ተወላጅ በተከፈተበት የማፈናቀል ዘመቻ ከሞት የተረፈው ሁሉ  ቤት ንብረቱን አጥቶ በጭፍና ክረምት በላስቲክ መጠለያ እና በየዛፉ ስር ነፍሱን ለማቆየት ተገድዶ ነበር፡፡ የስደተኛው ሰቆቃ፤ ረኀብ እና እርዛቱ ከለጋሾች ዕይታ እንዲሰወር ተደርጎ መቆየቱም ከማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ ይህ ሁሉ ኢሰብዓዊነት ለምን አስፈለገ?  ተዋድደህ እና ተዋልደህ ለዘመናት አብረህ ከኖረከው የጉጂ ማኅበረሰብ ጋር ግጭት ውስጥ የከተተህ ማን፤ የማፈናቀሉ ዓላማ እና ግብ ምንድን ሊሆን ይችላል? ያን ግፍ የፈጸሙብህ ወንጀለኞች የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ወጥቶባቸው እንኳን በሕግ እንዲጠየቁ አሳልፎ መስጠት ያልተፈለገው ስለ ምንድን ነው? ያን መከራ ያወረደብህ አገዛዝ ያሰማራቸው ወንጀለኞች ከፍትሕ አደባባይ ለመቅረብ አሻፈረኝ ያሉት ምንድን አስበው ነው? ራሳቸውን ከሕግ በላይ አድርገው የሚቆጥሩት አፈናቃዮችህ ዛሬስ ምን እያሴሩብህ ይሆን? መከራው ሰፍቶና ከፍቶ ተመልሶ እንደማይመጣብህ ምን ዋስትና አለህ?

የጋሞ ሕዝብ ሆይ፡-ለልማት እና ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄዎችህ ተገቢውን ምላሽ ከመስጠት ይልቅ እስር ፤ አፈና እና ግድያ የሚደገስልህ ስለምንድን ነው? የ2010 ዓ.ም የገዥዎች ለውጥ ተከትሎ የመጀመሪያውን የመከራ ገፈት ቀማሽ እንድትሆን የተደረገው ስለምንድን ይሆን? ቡራዩ እና ሰበታ ላይ የፈሰሰው ደምህ ዛሬም ስለፍትሕ ወደ አርያም ይጣራል፡፡ አገርህ ውስጥ አገር የሌለው ተደርገህ ሲያበቃ ከአዲስ አበባ እና ዙሪያዋ በሺህዎች አፈናቅለው ሜዳ ላይ ጣሉህ፡፡ ይህም አልበቃ ብሏቸው በነጭ ሣር ብሔራዊ ፓርክ በኩል ወሰን እያሰፉ አርባ ምንጭን በቅርብ ርቀት ከበባ ውስጥ ሊያስገቧት እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ ይህ የእነ ዋጠው አገዛዝ በዚህ ባሕርይው ከቀጠለ የጋሞ ሕዝብ ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል? ለባርነት መዘጋጀት ወይም አርነትን መቀዳጀት መንታ መንገድ ላይ!

የሸካ ሕዝብ ሆይ፡- አንተ ጥንቱንም ተክደህ ታውቀዋለህ፡፡ የክህደቱን ሕመም በሥነ ቃል ጭምር ከልጅ ልጅ እያስተላለፍክ ዘልቀሃል፡፡ በሰሜን አቅጣጫ ባሮ ቀላ የተፈጥሮ ወሰን ሆኖ ገላግሎሃል፡፡ በምዕራብ በኩል ግን ለዘመናት በሞቻ አውራጃ ግዛት ስር ይተዳደር የነበረውን ሰሌ ኖኖ ወረዳን እንድታጣ ተደርገሃል፡፡ ከማዣንግ ጋር ለምን በጠላትነት እንድትተያዩ እንደሚፈለግ የአገዛዙ ድብቅ አጀንዳ ምን እንደሆነ አይታወቅም፡፡ ቴፒ እና ሜጢ  የእርስ በእርስ ግጭት የስበት ማዕከል ሆነው የሚዘልቁትስ እስከ መቼ ነው? በገዛ አገርህ እንደ ሁለተኛ ዜጋ ተቆጥረህ በመሳቀቅ የምትኖረውስ እስከ መቼ ድረስ ነው?

የአማሮ ሕዝብ ሆይ፡-መግቢያ መውጫ ተዘግቶብህ የምትሰቃየው ምን በደል ስለፈጸምክ ይሆን? አቤቱታህ ሰሚ ጆሮ አጥቶ ነጋ ጠባ ትዘረፋለህ፤ ነጋ ጠባ ትገደላለህ፡፡ ወጥቶ ለመግባት እና ሠርቶ ለመብላት ዕድል የነፈገህ አገዛዝ ይባስ ብሎ ወሰን እየገፋ ያፈናቅልሃል፡፡ ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ የአማሮ ሕዝብ ሕልውና ጸንቶ ይዘልቅ ይመስልሃል?

የቡርጂ ሕዝብ ሆይ፡- አገዛዙ ከዓመት ዓመት ግጭት ይደግስልሃል፡፡ ሰዎችህ ይገደላሉ፡፡ ኃብት ንብረትህ ይዘረፋል፤ የተረፈውም ይወድማል፡፡ በደልህን ባታውቀውም ሁሌም የስጋት እና የሰቀቀን ኑሮ ለመምራት ትገደዳለህ፡፡ ኧረ ለመሆኑ፤ በገዛ አገርህ ባይተዋር ሆነህ እንዴት ትዘልቀዋለህ?

የመከላከያ መኮንኖች እና የሠራዊቱ አባላት ሆይ፡- የመከላከያ ሠራዊት ዓላማው የአገርን ዳር ድንበር ከጠላት ወረራ መጠበቅ ነው፡፡ የሠራዊቱ ታማኝነት ለባንዲራው፤ ታዛዥነቱም ለሕገ-መንግሥቱ እንደሆነ ይታመናል፡፡ ሠራዊቱ የጥቂት ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ሥልጣን ማስጠበቂያ አንጋች አይደለም፡፡ ከበላዮቹ የሚቀበለው ትዕዛዝም ቢሆን ከሕግ እና ከሕሊና መርህ ያፈነገጠ መሆን የለበትም፡፡ ገዥዎች የሚወዱትን እየወደደ እና እነርሱ በሚጠሉት ላይ ሣንጃ በአፈሙዝ እየወደረ የጥፋት ተልዕኮ አስፈጻሚ መሆን የለበትም፡፡ ጠንካራ መከላከያ የሚገነባው በተከታታይ የሙያ ላይ ስልጣና፤ በግዳጅ አፈጻጸም ብቃት እና ሥነ-ምግባር፤ እንዲሁም  በዓመታት ከሚካብት ተግባራዊ ልምድ እንጂ በተዋጊ ቁጥር ብቻ አይደለም፡፡ ሠራዊቱን መቅኖ ከሚያሳጡት መካከል አሸናፊ እና ተሸናፊ የሌለበት የእርስ በእርስ ጦርነት ነው፡፡ በኤርትራ ምድር ለ30 ዓመት፤ ከወያኔ ጋር ለ17 ዓመት፤ በባድመ ግጭት ከዓመት ባነሰ ጊዜ፤ ካለፉት አምስት ዓመታት ጀምሮ ከኦሮሞ ነጻ አውጭ ታጣቂዎች ጋር፤ ከሕወሓት ጋር ለሁለት ዓመት፤ አሁን ደግሞ በአማራ ክልል በመካሄድ ላይ በሚገኘው ነገር ግን በንግግር ብቻ እልባት ማግኘት ይችል በነበረ ጦርነት ለቁጥር የሚታክት መለዮ ለባሽ ወድቋል፡፡ ምናልባትም ቁጥሩ በሚሊየኖች የሚገመት፡፡ የዚያኑ ያህል ንጹኃን እህት እና ወንድሞቻችሁ አካላቸውን እና ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡ ያለ ባል የቀሩትን ሚስቶች፤ ያለ አባት የቀሩትን ልጆች፤ ያለ ጧሪ እና ቀባሪ የቀሩትን እናቶች እና አባቶች ቤቱ ይቁጠራቸው፡፡

ልጆቿ ጎራ ለይተው ሲተላለቁ እናት አገራችሁ ኀዘኗ ይከፋል፡፡ ሰው ወንድሙን እና እህቱን ገድሎ ጀግና አይባልም፡፡ ገዳይ እና ሟች የአንድ እናት ልጆች በሚሆኑበት ጊዜ አገር እጥፍ ድርብ ኪሣራ ላይ ትወድቃለች፡፡ እንዲህ ባለው ሁኔታ እናት ኢትዮጵያ የአብራክ ክፋይ ልጆቿን እና ጥሪቷንም ታጣለች፤ ታሟጥጣለች፡፡ በውጤት ርቀት ላይ ያነጣጠራችሁበት ሰው ወንድማችሁ መሆኑን አስቡ፡፡ የጠመንጃችሁን ቃታ ከመሳባችሁ በፊት የምትሞቱት እና የምትገድሉት ስለምን ዓላማ እንደሆነ ቆም ብላችሁ ጠይቁ፡፡ በእናንተ መስዋዕትነት የቤተ-መንግሥት ቆይታቸውን ለሚያመቻቹ የሥልጣን ጥመኞች ደባ እንዳትታለሉ ተጠንቀቁ፡፡ ገዥዎች ያልፋሉ፡፡ አገር እና ሕዝብ ግን ይቀጥላሉ፡፡

***

ጠቃለል፤ ባለፉት 32 ዓመታት የማዕከላዊ መንግሥቱን መንበር የተቆጣጠሩት ገዥዎች የስልት እንጂ የግብ ልዩነት የላቸውም፡፡ ሕወሓትም ሆነ ኦሕዴድ የአንድ ሣንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው፡፡ የሁለቱም ሕልም ከተሳካላቸው በአገር በቀል ቅኝ አገዛዝ ዘይቤ የተቀረውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰጥ ለጥ አድረገው ቀጥቅጠው ማስገበር ነው፡፡ ይህ የማይሳከ ከሆነ ደግሞ ከየክልሉ ያማራቸውን አካባቢ ሊያዋልዱ ተስፋ ወደሚያደርጉት አዲስ አገር ካርታ በማካተት እና መሬቱን ከነሕዝቡ ወይም ያለሕዝቡ ወደ ግዛታቸው መጠቅለል፡፡ የጊዜው ጥያቄ ይህ ነው፤ ለባርነት እጅ መስጠት ወይስ ለጸና ሉዓላዊነት፤ ለፍትሕ፤ ለዴሞክራሲ እና ለእኩልነት እጅ ለእጅ ተያይዞ የተደቀነብንን አደጋ በኅብረት መመከት?