ኢትዮጵያ በምትገነባው ግድብ ላይ ዋና የሚባሉት ሦስቱ የአባይ ተፋሰስ ሀገራት ዳግም  ለድርድር መሰብሰባቸው ተገለጸ።ኢትዮጵያ፣ግብጽ እና ሱዳን ለዓመታት የዘለቀውን ውይይት በዛሬው እለት በካይሮ እንደቀጠሉ ይፋ ያደረገው የግብጽ መስኖ ሚኒስትር ነው።
ባሳለፍነው ወር የሱዳንን ግጭት ለመፍታት በነበርው የአፍሪካ ሀገራት ስብሰባ ላይ የተገናኙት የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ኢቢይ አሕመድ እና የግብጹ አቻቸው አብደል ፈታህ አል-ሲሲ የግድቡ ውዝግብ በአራት ወራት ውስጥ እልባት እንደሚያገኝ መግለጻቸው ይታወሳል።
ኢትዮጵያ ግድቡን መጀመሯን ካሳወቀችበት ጊዜ ጀምሮ ሦስቱ ሀገራትን ሲያወዛግብ ቆይቷል። ግብጽ የአባይ ግድብ የውሃ ፍሰቱን በማስተጓጎል ለሕልውናዬ አደጋ ያመጣል በሚል ግንባታውን ለማስቆም ከድርድር ባለፈ ኢትዮጵያ ላይ ዓለምአቀፋዊ ጫና  ለማሳደር በርካታ ጥረቶችን ታካሄዳለች።ኢትዮጵያ ለግድቡ የሚውል የብድር ገንዘብ አንዳታገኝ ኃያል ሀገራትን ከመማጸን በተጨማሪ  ዓለምአቀፍ ተቋማትን ትወተውታለች።ከዚያም ባለፈ በቅኝ ግዛት ዘመን ከሱዳን ጋር በአባይ ወንዝ ላይ ያደረጉት የግብጽን የበላይነትና ፍጹም ውሳኝነትን የሚገልጸውን ስምምነት አንዲጸና ደጋግማ ለማሳሰብ ሞክራለች።
ኢትዮጵያ በበኩሏ ግድቡ የውሃ ፍሰትን የማያስተጓጉልና ለሱዳንም ሆነ ለግብጽ ስጋት እንደማይሆን አጽናኦት ሰጥታ ስትገልጽ ከርማለች። የአባይ ውሃ 80 በመቶው ከኢትዮጵያ የሚገኝ በመሆኑ ከውሃው የመጠቀም ተፈጥሯዊ መብት እንደሆነ በተለያዩ ልኡኮቿ በማስገንዘብ የግድቡን ግንባታ ቀጥላለች።
በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የስልጣን ዘመን የተጀመረው የሕዳሴ ግድብ በኢትዮጵያዊያን አቅም ብቻ ተገንብቶ በ5 ዓመታት ውስጥ አንደሚጠናቀቅ ቢገለጽም ከእጥፍ ጊዜ በላይ በመውሰድ እስካሁን ድረስ ሳይጠናቀቅ ቅርቷል።በፕሮጀክቱ ጅማሬ 4.5 ቢሊዮን ዶላር ይወስዳል የተባለው ይኸው ግድብ በታቅደለት የጊዜ ገደብ ባለመጠናቀቁ የወጪ ዋጋ ንረት ተከትሎበታል።
ይሁን አንጂ ኢትዮጵያ ያልውን ጫና ተቋቁማ የግድቡን ከ80 በመቶ በላይ ከማጠናቀቅ ባላፈ የግብጽና ሱዳንን ያለእኛ እውቅና ፈጽሞ መካሄድ የለበትም ያሉትን የውሃ ሙሌት በተሳካ ሁኔታ አከናውናለች።
ከሱዳን በ45 ኪሎ ሜትር ብቻ ርቀት ላይ እየተገነባ የሚገኘው ግድብን በተመለከተ ካይሮ ላይ እየተደራደሩ መሆናቸውን የገለጹት የግብጽ መስኖ ሚኒስትር ሀኒ ሴዊሰላም “የተጀመርው ድርድር የሦስቱን ሀገራት ፍላጎትና ስጋት ከግምት አስገብቶ በመነጋገር ከስምምነት ለመድረስ ያለመ ነው” ብለዋል።