የሻው ስንሻው

ነሐሴ 16/2015 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ

ለክብርት ሣህለወርቅ ዘውዴ፤ የኢፌዲሪ ፕረዚደንት

ለክቡር ዶ/ር ዐብይ አሕመድ፤ የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር

ለክቡር አቶ ደመቀ መኮንን፤ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር

ለክቡር አቶ ታገሰ ጫፎ፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ 

ለክቡር አቶ አገኘሁ ተሻገር፤ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ 

 

ክብርት እና ክቡራን፤ 

ለመሆኑ የአማራ ሕዝብ መፈናቀል፤ መሳደድ፤ እሮሮ እና እልቂት ማብቂያ የሚያገኘው መቼ ነው?

ይህን ደብዳቤ ስጽፍላችሁ ትኩረቴ በሰነድ ተደግፎ እና የፖለቲካ መርኃ-ግብርም ተነድፎለት እየተካሄደ ስለዘለቀው እና ማባሪያ ስለታጣለት በአማራ ሕዝብ ላይ  ስለሚፈጸመው ግፍ ነው፡፡ ግፉ ማኅበራዊ፤ ኤኮኖሚያዊ፤ እና ፖለቲካዊ ገጽታዎች እና መገለጫዎች ያሉት ቢሆንም የደብዳቤዬ ዋና ጭብጥ የአማራን ሕዝብ ሕልውና በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ይበልጥ አጽንዖት ይሰጣል፡፡ ይህንን ርዕሰ ጉዳይ ሳነሳ ግን አንድ ነጥብ ላይ እንዲሰመርልኝ አበክሬ እጠይቃለሁ፡፡ እርሱም፤ ዛሬ ላይ ያለችው ኢትዮጵያ ለአማራ ብቻ ሲዖል ለተቀረው ኢትዮጵያዊ ግን ገነት እንደሆነች አድርጌ የማስብ አለመሆኔ እንዲታወቅልኝ እፈልጋለሁ፡፡ 

እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡ የኢትዮጵያውያን ወገኖቼ ደስታ ያስፈነጥዘኛል፤ ሕመማቸውም አብዝቶ ይሰማኛል፡፡ የኦሮሞን ጉስቁልና፤ የሶማሌውን ፈተና፤ የሲዳማውን ጫና፤ የትግሬውን ሕመም፤  የአፋሩን መቆዘም፤ የጉራጌውን እመቃ፤ የጋሞውን ሰቆቃ ፤ የኮንሶውን ሲቃ፤ የጌዴኦን ጉዳት፤ የከምባታውን ምሬት፤ የሐዲያውን ጭንቀት፤ የወላይታውን ብሶት፤ የአማሮን ጩኸት፤ የደራሼን መገፋት፤ የአሌን መከፋት፤ የአኙዋክን ጭፍጨፋ፤ የማዣንግን ጥሪት ጥንፈፋ፤ የቡርጂን ሰቀቀን፤ የቁጫን ሕዝብ ወከባ፤ የአደሬን ከበባ፤ የኢሮብን አፈና፤ የኩናማን ገና ለገና፤ የስልጤን ተቃውሞ፤ የሀላባን አርምሞ፤ ወዘተርፈ  ራሳችንን ለማታለል ካልከጀለን በስተቀር ሁላችንም ጠንቅቀን እናውቀዋለን፡፡ እዚህ ላይ በፖለቲካ መሰሪነት ሳይሆን በኢትዮጵያዊ ቅንነት የምትምልሱልኝን አንዲት ጥያቄ ልሰንዝር፡፡ እንዲያው ለመሆኑ፤ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በወንድማማችነት፤ በእኩልነት እና በነጻነት ኮርተው የሚኖሩባት፤ ማንም ከሚገባው በላይ የማይጠይቅባት፤ ማንም ደግሞ የሚገባውን የማይነፈግባት አገር እንድትኖረን ለማስቻል ምንድን መደረግ ያለበት ይመስላችኋል?

ክብርት እና ክቡራን ሆይ፤ 

ለመሆኑ የአማራን ሕዝብ ማለቂያ በታጣለት መከራ ውስጥ እንዲያልፍ የሚደርገው ምንድን የተለየ ፍላጎት ኖሮት ወይም ምን ዓይነት በደል ቢገኝበት ነው? ለአገር ክብር ሲባል በየዘመኑ ከተነሱት ወራሪዎች ጋር አንገት ለአንገት ተናንቆ በመውደቅ አርነትን ማጽናቱ  እንደ ወንጀል ተቆጥሮበት ይሆንን? በአገር ውስጥ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ውስጥስ ቢሆን አማራ ከመጀመሪያው ረድፍ ላይ የታጣበት ጊዜ ይኖራልን? ለ1966 ሕዝባዊ አብዮት እርሾ የሆነውን የ1953ቱን የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ያቀዱት፤ ያስተባበሩት እና ከፊት ለፊት ሆነው የመሩት እነማን ነበሩ? የ66ቱን አብዮት ፋና ወጊ ሆነው ከአቀጣጠሉት  ኢትዮጵያውያን መካከል የአማራው ማኅበረሰብ ድርሻ የቱን ያህል እንደሆነ ይዘነጋልን? የደርግን አገዛዝ ለማስወገድ በተደረገው ፍልሚያ ውስጥ የአማራው ተሣትፎ ምን ይመስል እንደነበር ለመገንዘብ ከእናንተ የተለየ እማኝ ያሻዋልን? የግፍ ጽዋው ሞልቶ ሕወሓት በማዕከላዊ መንግሥት ውስጥ የነበረውን የአድራጊ ፈጣሪነት ሚና እንዲያጣ ሲደረግ ለለውጡ እውን መሆን ሲባል የአማራ ሕዝብ የውድ ልጆቹን ሕይወት አልገበረምን? ይህ ስለመሆኑ አሁን ሥልጣን ላይ ያላችሁት እናንተ የዓይን እማኞች አይደላችሁምን?

እንግዲያውስ፤ አማራ በማንነቱ የተነሣ በእናት አገሩ ውስጥ መጻተኛ፤ ባይተዋር እና ጠላት ተደርጎ የሚቆጠረው ስለምንድን እና እስከ መቼ ድረስ ነው? እስኪ ጥያቄዎቼን በፈርጅ በፈርጁ እንደሚከተለው አድርጌ ላቅርብ፡- 

 1. ለመሆኑ እናንተ የምትመሩት መንግሥት አማራን በጠላትነት ስለሚፈርጀው እና በሚበዙቱ የዘውግ አስተሳሰብ አራማጅ ፖለቲከኞች ዘንድ በገቢርም በሐቲትም እንደ ቀኖና የሚቀነቀነው የ1968 የሕወሓት ማኒፌስቶ ይዘት እንዲታረም እና መነሻ እና መድረሻውም እንደ ገና እንዲጤን ተጠይቆ ያውቃልን? እንግዲያውስ፤ የአንድን አገር ሕዝብ በጠላትነት እና ወዳጅነት የሚፈርጅ የፖለቲካ አስተሳሰብን በጉያ ሸጉጦ ሚዛናዊ እና የሁሉም ሕዝብ እኩል መሪ መሆን ይቻላልን?
 2. እስኪ እውነት እውነቱን እንነጋገር፡፡ የመገንጠል ዓላማ አራማጆችን ጎጆ ለማውጣት ሲባል በኢትዮጵያዊነት ማተቡ የጸናው የአማራ ሕዝብ ከአጽመ እርስቱ መነቀል አለበትን? ከሱዳን ጋር ቀጥታ የሚያገናኝ መንገድ በመጥረግ እና ኢትዮጵያ ፈራርሳ ለምትመሠረተው ሪፐብሊክ ለም የእርሻ መሬት ለማግኘቱ ትልም ካልሆነ በስተቀር እውን ሕወሓት የወልቃይትን ጉዳይ ነክሶ የያዘው የትግራይ እና የጎንደር ወሰን ተከዜ መሆኑ ጠፍቶት ነው? የራያ ጉዳይስ ቢሆን? ሕወሓት ይህን ሁሉ ትርምስ የሚፈጥረው ገሐድ ለወጣው የመገንጠል አጀንዳው ማስፈጸሚያነት ካልሆነ በስተቀር ከሕወሓት በፊት የነበረው እና ከሕወሓት በኋላም የሚኖረው ኢትዮጳያዊው ትግራዋይ በአገሩ ውስጥ በመረጠበት ስፍራ ኑሮውን ቢመሠርት ማን ቀና ብሎ ያየዋል? ከሰሞኑ ሕወሓት በጉልበት የጠቀለለው ይዞታ ጉዳይ በሕገ መንግሥቱ መሠረት “በሕዝበ ውሣኔ ምላሽ ያገኛል” የሚሉ ቀጫጭን ድምጾች እየተደመጡ ናቸው፡፡ ሐሳቡ ባልከፋ ነበር፡፡ ነገር ግን፤ ሕገ መንግሥቱ ከመረቀቁ እና ከመጽደቁ በፊት በፎርሳ ለተጠቀለለ ግዛት የአማራ ሕዝብ ይሁንታ የሌለው ሕገ መንግሥትስ ቢሆን እንዴት የመፍትሔ አካል ተደርጎ ሊቆጠር ይችላል? ለመሆኑ ሕገ መንግሥቱ ራያን እና ወልቃይትን ለሕወሓት የሸለመው በየትኛው አንቀጹ ይሆን? ሕገ መንግሥታዊ ግዛት ሕገ መንግሥታዊ ድጋፍ ሊኖረው አይገባምን? የሕወሓት ፍላጎት በራሱ እንደ ሕገ መንግሥት ይቆጠር ከተባለ እርሱ ሌላ ጉዳይ ነው፡፡ ሕዝበ ውሣኔስ ቢባል በሕዝበ ውሣኔው የሚሳተፈው ማን ነው? እዚህ ላይ አንዲት አብነት ልጥቀስ፡፡ ሕወሓት በፊታውራሪነት ያስፈጸመው የ1985 የኤርትራ ሕዝበ ውሣኔ ትዝ ይላችኋል አይደል? ከ”ባርነት እና አርነት” እንዲመርጡ የተጠየቁት የጉዳዩ ባለቤቶች የኤርትራ ተወላጆች ብቻ ነበሩ፡፡ ዛሬም የተበደለው፤ የተገደለው እና አረዳውን የተነጠቀው ሕዝብ እንጂ በዳይ፤ ገዳይ እና አሳዳጁ የአማራን ሕዝብ ዕድል በእንበለ ሕዝበ ዉሣኔ ሽፋን “እንብላ ካላችሁም እንብላ፤ አንብላ ካላችሁም እንብላ” እንዲለን መፍቀድ አይኖርብንም፡፡ ልክ ነኝ?
 3. በ1970 መባቻ ግድም የወልቃይት ወንዶችን በስውር ማጎሪያዎች እያሰቃዩ እና እየገደሉ ሚስቶቻቸውን ወርሶ በማስወለድ የተወጠነው እና በ1982 ዓ.ም ወደ አሶሣ ተሻግሮ ምስኪን የአማራ ተወላጆችን ቤት ውስጥ ቆልፎ ቤንዚን አርከፍክፎ በእሳት ቃጠሎ በመፍጀት የተቀጣጠለው ማንነት ላይ ያነጣጠረው፤ በሰብዓዊ ፍጡር ላይ የሚፈጸም ወንጀል ዛሬ ላይ የት እንደደረሰ ለመገንዘብ አሁን ያለው አገዛዝ አስታዋሽ አስፈልጎት ይሆን? እናንተ ወደ ሥልጣን በመጣችሁ ማግስት በሐረርጌ የተለያዩ አካባቢዎች፤ በሻሸመኔ፤ በአርሲ ነገሌ፤ በኮፈሌ፤ በዶዶላ፤ በአጋርፋ፤ በሁሩታ፤ እና ሌሎችም አጥቢያዎች ላይ የተፈጸመውን ማንነት ተኮር ግድያ፤ የንብረት ውድመት እንዲሁም አጽምን ማሳረፊያ የማሳጣትን አስነዋሪ ተግባር አምርሮ ለማውገዝ እንኳን ድፍረቱ ነበራችሁ ወይ? በአማራ ሕዝብ ላይ በቆቦ፤ በአጋምሣ፤ በጭና ተክለ ኃይማኖት እና  በማይ ካድራ የተፈጸመውን የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ የዝምታ ቡራኬ ሰጥተን ሲያበቃ እንዲቀጥል አላበረታታንም ለማለት የሞራል ብቃቱ ይኖረን ይሆን? ይህን መሰል ተናባቢ እና ቀጣይ ጥቃትም ቢሆን ቀደም ሲል ከተነደፈው አማራን ጠልቶ ከማስጠላት እና ማኅበረሰብዓዊ እረፍት ከመንሳት ፍኖተ ካርታ የተቀዳ ላለመሆኑ አፍራሻውን የሚጠቁም አንዳች ማረጋገጫ ሊቀርብ ይችላልን?  
 4. የሌላ ማንነት ካባ የተደረበለት እና የዘር ፍጅት የተደገሰለት የወልቃይት እና የራያ ሕዝብ ስደት እና ሞት እውን ሰሚ ጆሮ አግኝቷልን? እንዲያው ለነገሩ፤ የሰውን ልጅ ማንነት የሚወስንለት ማን ነው? መሬቱ ስለሚፈለግ ብቻ የማይፈለግ ማንነት ያለው ሁሉ ከምድረ ገጽ እስኪጠፋ ድረስ መታገስ ይጠበቅብን ይሆን? መከራው ማክተሚያ አስካልተገኘለት ድረስ ነጋ ጠባ በሞት ጥላ ስር ለሚመላለሰው ለመከረኛው ሕዝብ “እስክታልቁ ታገሱ” ተብሎ ቁርጡ ቢነገረው ይሻል አይመስላችሁምን? ውሳኔያችሁ እንዲህ ያለ ባይሆን ኖሮ ለወልቃይት እና ለራያ ሕዝብ ከሁለት ዓመት በላይ በጀት በመከልከል ስለምን መሠረታዊ አገልግሎት ተነፍጎት በቸነፈር  እና በደዌ እንዲፈተን ታደርጉታላችሁ? 
 5. የ1983 የሽግግር አስተዳደር ሰነድ ሲጸድቅ በጉባዔው ላይ አማራ ተወካይ እንዳይኖረው ተደረገ፡፡ ይህ ድርጊት የልብ ልብ የሰጣቸው ጥላቻ አቀንቃኞች በአርባ ጉጉ፤ በወተር፤ በበደኖ፤ በአሰቦት ገዳም እና ሌሎችም አካባቢዎች በአማራ ተወላጅ ኢትዮጵያውያን ላይ የተፈጸሙት ዘግናኝ የግፍ ጭፍጨፋ ከቶውንም መዘንጋት የማይችል የታሪክ ጠባሳችን አይደለምን? እንደ መሠረተ-ቢስ ውንጀላው እና ጉንጭ አልፋ ትርክቱ ቅብብሎሽ ዐፄ ምንሊክ “በድለዋል” ብንል እንኳን ንጉሠ ነገሥቱ በሥልጣን ላይ የቆዩት ለ24 ዓመት ሲሆን አማራን የማሳደዱ እና በተገኘበት “የማርያም ጠላት” የማሰኘቱ ተግባር ግን እነሆ ሕወሓት ወደ ደደቢት ካቀናበት ዘመን ጀምሮ ሲሰላ አሁን 48 ዓመት ሞላው፡፡ ለመሆኑ አማራ ያልተበደረውን የመከራ ዕዳ እየገፈገፈ የሚዘልቀው እስከ መቼ ድረስ ነው? 
 6. ከክልሉ ውጭ የሚገኝ የአማራ ተወላጅ በሚኖርበት አካባቢ የቱን ያህል ከፍ ያለ ቁጥር ቢኖረውም ራሱን ለማስተዳደር የመጠየቅ መብት እና የፖለቲካ ውክልና  አልተነፈገምን?  ከማንነቱ የተነሳ የሰው ሲሶ ተደርጎ ሲያበቃ ሦስት አማራ እንደ አንድ ሰው እንዲቆጠር ያለአንዳች እፍረት አልተበየነምን?  ድሬ ዳዋ ከተማ ውስጥ የነዋሪውን አርባ ከመቶ የሚሸፍነው ሕዝብ አማራ በመሆኑ ብቻ ከተማዋ መሬት ላይ ከሚታየው እውነት ፈጽሞ በተቃራኒው አቅጣጫ አልተኼደም? ይህ ድርጊት ከምድርም አልፎ በሠማይ የሚያስጠይቅ በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል አይደለምን? 
 7. በኢትዮጵያ ግዛት የተለያዩ ክፍላተ አገር ኑሮዉን የመሠረተው እና በዚያ ከአንድም ሦስት አራት ትውልድ ያስቆጠረው የአማራ ተወላጅ በኢትዮጵያዊ ዜግነቱ የፖለቲካ ተሣትፎ ውክልና ከመነፈግም አልፎ ተረፎ ላቡን አንጠፍጥፎ ያፈራውን ጥሪት እየተነጠቀ በአካባቢያዊ አስተዳደር ቀላጤ ጭምር ከመኖሪያው ሲፈናቀል፤ ሲሳደድ እና መግቢያ ያጣ ከርታታ እንዲሆን ሲፈረድበት ‘አላየንም አልሰማንም’ ልንል እንችል ይሆንን?
 8. የማግለሉ፤ ማፈናቀሉ እና የመግደሉ ግፍ ማቆሚያ ታጥቶለት ቀጥሎ ሳለ በአማራ ክልል ውስጥ የሚገኝ 3 ሚሊየን ከሕዝብ እና ቤቶች ቆጠራ መዝገብ ላይ እንዳይታይ ተደርጎ ለአንድ የምርጫ ዘመን ጤና እና ትምህርትን ጨምሮ  የትኛውንም ዓይነት የመንግሥት መሠረታዊ አገልግሎት እንዲያጣ ሲደረግ ከዚህ የከፋ ሕጋዊ ሕገ ወጥነት እና መረን የለቀቀ በደል ይኖር ይሆን?
 9. ከ1980 አካፋይ አንስቶ የወለጋ ምድር በአማራ ተወላጆች ደም እየጨቀየ እስከ አሁን ድረስ አልዘለቀምን? ለመሆኑ አንድን ሕዝብ በማንነቱ የተነሳ ርዝራዡን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት ለምን ያህል ጊዜ መታገስ ይኖርብን ይሆን? ከናዚ የአይሁዳውያን ጅምላ ፍጅት (Holocaust) በኋላ በአጭር ጊዜ ብዙ ሰው (እስከ አንድ ሚሊየን የሚገመት) የተፈጀበት የሩዋንዳው ማንነት ተኮር ጭፍጨፋ ነበር፡፡ በኢትዮጵያችን እኮ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ብቻ ከሚሊዮን በላይ ዜጎች አልቀዋል፡፡ ይህን መከራ ለመሻገር ከዋሻው የወዲያኛው ጫፍ ቅንጣት የብርሐን ጭላንጭል እንኳን አልታይህ ካለኝ ሰነባብቷል፤ እናንተስ? 
 10. እናት እና አባት “ልጆቼ ተምረው ያልፍላቸዋል፤ እኔንም ያሳርፉኛል” በሚል ተስፋ ወደ ደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ቤት ያፈራውን ሰንቆ እና በአገር ባሕል መርቆ የሸኛቸው ልጆቹ ተጠልፈው ደብዛቸው ሲጠፋ ወጣቶቹ ከአማራ ቤተሰብ ከመወለድ ሌላ ምንድን ወንጀል ተገኝቶባቸው ይሆን? ለመሆኑ፤ መንግሥት ይህን ጉዳይ በተመለከተ “የውሾን ስም ያነሳ ውሾን ይሁን” ማለት የመረጠ የሚመስለው ለምንድን ነው?
 11. መተከል ላይ ምናልባትም በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሊያስብል በሚያስደፍር መልኩ የአማራ ተወላጆች ለአሰቃቂ ጭፍጨፋ ከመዳረጋቸውም ባሻገር አስከሬናቸው እንኳን ሰብዓዊ ክብር ተነፍጎት በግሬደር እየተገፋ  ወደ ተረተር እና ፈፋ ሲወረወር ከማየት ያለፈ ሰው መሆንን የሚያስጠላ የሕይወት ዘመን ሰቅጣጭ ገጠመኝ ይኖር ይሆን?
 12. የአዲስ አበባ መግቢያ በሮች ለአማራ ተወላጅ እንዲከረቸሙ ሲወሰን እና ሰዎች ከመናገሻ ከተማቸው ብቻ ሳይሆን ከመኖሪያ ቤታቸው ተመልሰው እንዳይገቡ ሲደረግ ምናልባትም የክፍለ ዘመኑ ፖለቲካዊ ነውር አልተፈጸመምን? ለንግድ ሥራ የሚመላለሰውን፤ የሕክምና ቀጠሮ የነበረውን፤ ዓለም አቀፍ በረራ የተስተጓጎለበትን እና ሌላ ሌላውን ሁሉ ለጊዜው ልለፈው፡፡ አንዲት የአዲስ አበባ ነዋሪ ሴት ጡት የሚጠባ ጨቅላ ለጎረቤት አደራ ሰጥታ በወላጅ እናቷ ቀብር ላይ ለመገኘት ወደ ጎጃም ተሻገረች፡፡ ከቀብሩ ስትመለስ ወደ አዲስ አበባ ተመልሶ መግባት አልተፈቀደላትም፡፡ የእናት ጡት ወተት ብቻ የሚመገብ ሕጻን ትታ የሄደችው እመጫት እየተንሰቀሰቀች ስትለምን  እና የአዲስ አበባ ነዋሪነት መታወቂያዋን እያሳየች ስትማጸን አንዳች የሚራራ ልብ እና የሚሰማ ጆሮ አላገኘችም፡፡ ከዓይኖቿ እንባ ሲጎርፍ፤ የጡቷ ወተት ቁልቁል ይንዠቀዠቅ ነበር፡፡ እንዲህም ተደርጓል፤ እየተደረገም ይገኛል፡፡ ይህን አስጸያፊ ተግባር የፈጸምን፤ ያስፈጸምን እና ዳር ቆመን የተመለከትን ጭምር ከፍትሕ አደባባይ የምንቀርብበት ጊዜ ቢርቅ እንኳ ከሕሊና ወቀሳ  እና ከታሪክ ተጠያቂነት የምናመልጥ  ይመስለን ይሆንን? 
 13. ኑሯቸውን ለማሸነፍ ደፋ ቀና የሚሉ ሰዎች በገፍ እየታገቱ በሚሊየኖች የሚቆጠር ገንዘብ በአጋቾች እየተጠየቁ የተሳካለት እርጥባን ጠይቆም ቢሆን ከፍሎ ሲለቀቅ፤ ወገን እና ጥሪት ያጠረው የውኃ ሽታ ሆኖ መቅረቱ የአማራ እናቶችን ቅስም መስበሩን ለመገንዘብ የተለየ ችሎታ የሚጠይቅ ጉዳይ ተደርጎ ይቆጠራልን? ለመሆኑ እንዲህ ያለው እገታ ሲዘወተር፤ የሰው እና የሸቀጥ ዝውውር ሲስተጓጎል፤ ዜጎች እንደወጡ ሲቀሩ፤ ሰዎች በሠራዊት ተገድለው በአራዊት ሆድ ሲቀበሩ፤ ይህ የኢትዮጵያውያን የዕለት ተዕለት ገጠመኝ ሲሆን መንግሥት አይቶ እንዳላየ፤ ሰምቶም እንዳልሰማ ከማለፍ የዘለለ ምንድን አደረገ?
 14. ጥቃቱ አማራ ተኮር ላለመሆኑ አንዳች አሳማኝ ማረጋገጫ ማቅረብ በማይቻልበት መልኩ (ሌሎች ሰለባዎች የሉም ማለቴ አይደለም) ሰዎች መኖሪያ ቤቶቻቸው እንዲፈርሱባቸው መደረጉ ሳያንስ ጎረቤት እንኳን እንዳያስጠልላቸው እንዲያም ሲል በማንኛውም ሁኔታ የቤት ኪራይ አገልግሎት እንዳይሰጣቸው መደረጉ እና መደንገጉ ከሰው አልፎ ሰብዓዊነትን መቃረን እና ማጥቃት አይሆንምን? በዚህ ሕገ ወጥ ድርጊት የተነሳ ጧት ከቤታቸው ወደ ትምህርት ቤት የተሸኙ ሕጻናት ከሰዓት በኋላ ሲመለሱ ቤታቸው ፈርሶ አልጠበቃቸውም? ይህ ለሕጻናቱ የዕድሜ ዘመን ሰቀቀን አይደለምን? ከኢሰብዓዊ ድርጊቶቻችን የተነሳ በእነዚህ አዳጊ ሕጻናት አዕምሮ ውስጥ ምን ዓይነት ምሥል እያስቀመጥን እንደሆነ ልብ ብለነዋል? ዜጎችን “ሕጋዊ ደኃ አደረግን” በማለት ከመመጻደቅ የተሻለ የልማት አማራጭ መንገድ መቀየስ ይቻል አልነበረምን? እንዲያው ለመሆኑ፤ ብልጽግና የሚረጋገጠው ድኅነትን በማጥፋት ወይስ ድኃ ዜጎችን በማሳደድ እና በማጥቃት?
 15. “ራሴን እና ቤተሰቤን ለማሰንበት፤ የተረፈኝን እህል ለከተሜው ቀለብ ላቀርብለት ማሣዬን አርሼ እና አለስልሼ ማዳበሪያ እና ምርጥ ዘር ቸገረኝ” በማለት ጅራፍ በማጮኽ ለጠየቀ ገበሬ መድፍ እና መትረየስ መስደድ መፍትሔ እንደማይሆን ለመረዳት ነብይ መሆንን ይጠይቅ አይመስለኝም፡፡ እውን ከማዳበሪያ እና ከምርጥ ዘር ይልቅ የድሮን፤ የባለስቲክ ሚሣኤል እና የመድፍ ጥይት ዋጋ ይረክሳልን?
 16. የአማራ ሕዝብ መከራው ተዘርዝሮ አያልቅም፡፡ ከክልሉ ውጭም በክልሉ ውስጥም ይበደላል፤ ይገደላል፡፡ የግድያ ሰለባዎቹ ሕጻናት፤ ወጣቶች፤ ባልቴቶች እና አዛውንቶች ጭምር ናቸው፡፡ ይህም አልበቃ ብሎ  ከቀጣዩ ትውልድ ዕድሜ ተበድረን፤ የነፍሰ ጡር ሆድ ተዘርግፎ ገና ወደ ምድር ያልመጣ ሽል ላይ ጭምር እንጨክናለን፡፡ የሰውን ልጅ ገድሎ ማቃጠልም ሆነ አቃጥሎ መግደል ተዘውታሪ ትዕይንቶች አልሆኑምን? በጠላትነት እሳቤ ማኅበረሰቡ ላይ ሥነ-ልቦናዊ እና አካላዊ ጥቃት ባለማቋረጥ በሚሰነዘርበት እና ከጦርነት ውድመት ከቶውንም ባላገገመበት ሁኔታ… ሚሊየኖች ተፈናቅለው የዕለት ጉርስ፤ የዓመት ልብስ እና አንገት ማስገቢያ ጎጆ በተነፈጉባት ምድር ሌላ እልቂት፤ ሌላ መፈናቀል እና ሌላ ስደት ለዚህ ሕዝብ ይገባዋልን?
 17. የአማራ ክልል በላይ በኩል በሱዳን ጦር (የሳምሪን ቡድን ጨምሮ)፤ በቤን ሻንጉል በኩል በጉሙዝ አማጽያን፤ በሸዋ እና በወሎ በኩል በኦሮሞ ነጻ አውጭ ግንባር፤ በሰሜን ምሥራቅ በኩል በትግራይ ነጻ አውጭ ግንባር ዙሪያውን ከበባ ውስጥ ገብቶ ከየአቅጣጫው ፍላጻ ይወረወርበታል፡፡ በክልሉ ውስጥ ደግሞ የአገው ሸንጎ እና የቅማንት ታጣቂዎች ጦር ሰብቀውበታል፡፡ ይባስ ብሎ ማዕከላዊው መንግሥት ከቅርብ ወራት ወዲህ ያለ የሌለ ኃይሉን አዝምቶበታል፡፡ የምጽዓት ቀን ካልሆነ በስተቀር የአማራን ሕዝብ ሕልውና አደጋ ላይ የሚጥል ከዚህ የሰፋ የመከራ መጠን እና ከዚህም የከፋ አስጨናቂ ዘመን ሊኖር ይችላልን? 
 18.  የአማራ ሕዝብ ባልመረጣቸው ምስለኔዎች እየተገዛ ፍዳውን ቆጥሯል፡፡ በመሠረተ ልማት ዝርጋታ ወደ ኋላ እንዲጎተት ተደርጓል፡፡ በክልሉ የመንገድ አውታር በበቂ ሁኔታ ባለመስፋፋቱ ዛሬም ሕሙማንን እና ወላዶችን በቃሬዛ የሳንሳ እየተሸከመ ያመላልሳል፡፡ አምራች ኢንዱስትሪ እንዳይስፋፋለት የመብራት አቅርቦት ጉድለት ያናጥርበታል፡፡ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ልጆቹ ፊደል የሚቆጥሩት ከጨፈቃ በተሠራ ዳስ እና በዛፍ ጥላ ስር ተሰባስበው እና ድንጋይ ላይ ተቀምጠው ነው፡፡ እንዲያው ለመሆኑ የዚህ ሕዝብ ብሶት የሚሰማችሁ መቼ ነው? አሁን ባለው አስተዳደር እና አስተሳሰብ የአማራ ሕዝብ ጥያቄ ምላሽ የሚያገኝ ይመስላችኋል? ከዚያስ?
 19. የሕወሓት መሪዎች ‘የአማራን አከርካሪ አውጥተን ጥለን ሲያበቃ ለእስክስታ የሚሆን ትከሻ ብቻ አስቀረንለት’ በማለት ተመጻደቁበት፡፡ የወር ተራው ደግሞ አሁን ያላችሁት ገዥዎች ሆነና “የአማራን ሕዝብ እንኳን ትጥቁን ገና ሱሪውን እናስወልቀዋለን” የሚል አቋም እንደምታራምዱ ሹክሹክታው መናኘት ይዟል፡፡ ትናንት “ማርከህ ታጠቅ”፤ ዛሬ ደግሞ “ምርኮህን ልንጠቅ” ማለት ምን ይሉት ክህደት እና ንቀት ነው? እውን እንዲህ ዓይነቱ አያያዝ የሥልጣን መንበራችሁን ያጸናላችኋል? ይህችን የፈረደባትን አገርስ ከተዶለችበት አረንቋ ያወጣታል? አገር ከሌለ ሥልጣን ይኖራልን? አሁን የመረጣችሁት መንገድ ኢትዮጵያን እንደ ገና ወደ ዘመነ መሣፍንት እንደማያንሸራትታት የቱን ያህል እርግጠኛ መሆን ትችላላችሁ? ይህን መሰሉ የኋሊት ጎዳና መታጠፊያው የት ላይ ሊሆን ይችላል? እንኪያስ፤ ከቁልቁለቱ ጉዞ ማን አትርፎ – ማን ይከስር፤ ማን ደኅይቶ – ማን ይከብር ይመስላችኋል? 
 20. የአማራ ሕዝብ የመብት፤ የእኩልነት እና የመልካም አስተዳደር እንጂ የዙፋን ጥያቄ የለውም፡፡ ደኀ እስካልተበደለ፤ ፍትሕ እስካልተጓደለ እና ምርጫው ዴሞክራሲያዊ መርህን የተከተለ እስከሆነ ድረስ ተመራጩ ኢትዮጵያዊ ይሁን እንጂ  ከቤተ- መንግሥት የሚገባው ማንም ይሁን ማን ይህ ለአማራው ጉዳዩ አይደለም፡፡ የአማራ ሕዝብ “በፈጠራ ትርክት ከወንድሞቼ ኢትዮጵያውያን አታለያዩኝ፤ አጎንብስና እንርገጥህም አትበሉኝ” አለ እንጂ ራሱን ከተቀረው ወገኑ አብልጦም ሆነ አሳንሶ አልተመለከተም፡፡ በኢትዮጵያ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ የነገሡት ዐፄ ኃይለሥላሴ (ተፈሪ መኮንን ወልደሚካኤል ጉዲሣ) ለረዥም ዘመን አገሪቱን የመሩት በኢትዮጵያዊነት እንጂ በአማራነት አልነበረም፡፡ ሌፍተናንት ጀነራል አማን ሚካኤል አንዶም፤ ብርጋዲየር ጀነራል ተፈሪ በንቲም ሆኑ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ወልዴ አያና የደርግን ላዕላይ መዋቅር ይመሩ የነበሩት በኢትዮጵያዊነት እንጂ በአማራነት አይደለም፡፡  የቀድሞዎቹ ጠቅላይ ሚኒስትሮች መለስ (ለገሠ) ዜናዊ አስረስ እና ኃይለማርያም ደሣለኝ ቦሼ አማራ አልነበሩም፡፡ የአማራ ሕዝብ (በአገር ውስጥ እና ባሕር ማዶ የሚኖረውም ጭምር) በነቂስ ወጥቶ ልባዊ ድጋፉን ቸሯቸው የነበረው የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ዓሊ አማራ ስለመሆን አለመሆናቸው ከገዛ ራሳቸው በላይ ነቃሽ አያሻውም፡፡ እንግዲያውስ፤ የአማራ ሕዝብ ጥያቄ “በአገሬ ባይተዋር አታድርጉኝ፤ አታሰቃዩኝ፤ የዜግነት መብት እና ሰብዓዊ ክብር አትንፈጉኝ፤ አታደኽዩኝ፤ አታፈናቅሉኝ፤ አትግደሉኝ” የሚል ሆኖ ሳለ የመድፍ እና መትረየስ እንዲያም ሲል የቦንብ እና አዳፍኔ ምላሽ የሚሰጠው ስለምንድን ነው? ከእንግዲህ ወዲያስ ቢሆን፤ እውን የአማራ ሕዝብ ከገራፊ ወደ ሌላ ገራፊ፤ ከዘራፊ ወደ ሌላ ዘራፊ  በመያዣነት ተላልፎ እየተሰጠ የሚቀጥል ይመስላችኋል?